Get Mystery Box with random crypto!

#ስጦታ አንድ ቀን ግን እናቴ ካለወትሮዋ ተለሳለሰች፡፡ በዚህ የባህሪ ለውጥ በጣም ነበር የተገረም | ግጥም፥ ትረካ ፥የፍቅር ደብዳቤዎች

#ስጦታ
አንድ ቀን ግን እናቴ ካለወትሮዋ ተለሳለሰች፡፡ በዚህ የባህሪ ለውጥ በጣም ነበር የተገረምነው፡፡ አንድም ቀን ስጦታ ሲሰጠንና ስንቀበል ፊቷ ተፈቶ የማያውቀው እናታችን፤ አጎታችን (ወንድሟ) ከልጆቹ ሁሉ ለይቶ ለእኔ ስጦታ ሊሰጠኝ ሲል ፈገግ አለች፡፡ከምር ፈገግ አለች! እሱ ስጦታውን ሲያወጣ፣የሆነች የተንኮል ፈገግታ ፊቷ ላይ አንዣበበች፡፡ እንዲያውም ጭራሽ “ምን ያቅደረድርሃል? ተቀበል! አጎትህ አይደል አለችን፡፡ የእናቴ ተንኮል የተገለጠልኝ በኋላ ነበር፡፡ ሴት መለኛ ናት የሚባለው የገባኝ በእናቴ ነው፡፡

አቤት የዚህ አጎቴ ስጦታ ሲገርም! ይኼ አጎታችን ገንዘብ ነፍሱ ነው፡፡ ማነት አይደለም፤ ለምሳሌ አጎታችን ሲራመድ ትንሽ ያነክሳል፡፡ወታደር ስለነበር አንዳንዶች ጦር ሜዳ ተመትቶ ይመስላቸዋል፡፡ እሱ እንደሆነ ከጦር ሜዳ የተመለሰው ጠላት ዝንቡን እሽ ሳይለው ነበር፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው! (እውነት ይሁን ውሸት ግን አላውቅም፤ ሲወራ ነው የሰማሁት) አንድ ቀን መንገድ ዳር እቃ ገዝቶ መልሱን ሲቆጥር፣ ስሙኒ ከእጁ አፈትልካ ትወድቃለች፡፡ ሣንቲሟ ስትንከባለል፣ አጎቴ አጎንብሶ ሲከተል ዘሎ መኪና መንገድ መሃል ይገባል፡፡ አጎቴ ስሙኒዋ ላይ ሳይደርስ ፣ሲግለበለብ የመጣ ታክሲ ቀኝ አግሩን አገኜው፤ ይኼው እስከ ዛሬ ያነክሳል፡፡ ታዲያ ይኼ አጎቴ አልፎ አልፎ ነው ስጦታ የሚሰጠን፡፡ እንዲያውም ስንቀልድ “የአጎታችን ስጦታ እንደ ፀሐይ ግርዶሽ በመቶ ዓመት አንድ ጊዜ ነው የሚከሰተው እንል ነበር፡፡ ለዚያውም ደግሞ ስጦታው ዝም ብሎ አይሰጥም፤ ሂደት አለው፣ማብራሪያ አለው፣መግለጫ አለው እና የዛን ቀን የሰጠኝ ስጦታ ትዝ ይለኛል! እቤታችን አራት ቀን ሰንብቶ በአምስተኛው ቀን ሊሄድ ሲነሳ “ኧረግ ረስቸው አቡቹ ና ስቲ ወዲህ ስጦታ ገዝቼልህ፣ረስቼ ተሸክሜው ልሄድ ነበር! አለ:: እኔ ደግሞ ለሸክም የሚበቃ ምን ጉድ አመጣልኝ ብዬ በግርምት መጠበቅ! መጀመሪያ እጁ ጋቢውን እየሰረሰረ ካፖርቱ ላይ ደረሰ፣ ካፖርቱን አልፎ ኮቱ፣ ኮቱን ሰርስሮ ከሸሚዙ ደረት ኪስ ውስጥ ምዝዝ አድርጎ፣ አንዲት ገና ያልተቀረጸች አዲስ እርሳስ አወጣ! በቃ እርሳስ ነበር ስጦታው፡፡ ያን ሁሉ ቁፋሮ ለተመለከተ፣ አጎቴ ነዳጅ የሚያወጣ ነበር የሚመስለው፡፡ “ይኼው….ይኼ ተላይ ያለው ማጥፊያው ነው(ይፈነዳ ይመስል በጥንቃቄ እየነካ)….አሁን __ የእርሳስ ማጥፊያ ምን ማብራሪያ ያስፈልገዋል? “በጣም አትፈግፍገው፤ ቶሎ ያልቃል፡፡ ደሞ ስተቀርጥ አባትህ በምላጭ ይቅረጥልህ፡፡ ይኼ ዘመን አመጣሽ መቅረጫ አንዴ ጠርቦ ነው የሚጥለው” ብሎ ከረዥም ምክር ጋር እርሳሷን ሰጠኝ፡፡ ይኼ ሲገርመኝ ከዚያን ቀን ጀምሮ ንዝንዙ በየት ይልቀቀኝ፡፡ እቤታችን በመጣ ቁጥር ሌላ ስጦታ የለም፡፡ “አቡቹ ያ ርሳስ ..እንዴት ነው? …ጥሩ እየተገለገልክበት ነው አዎ በጣም አትቅረጠው እንደነገርኩህ በምላጭ፣ሥዕል ደሞ ሣልበት ሥዕል ትልቅ ሙያ ነው… ለሥዕል ዋናው ነገር 'ርሳስ ነው፣ 'ርሳስ ካለ ሥዕል አለ፡፡ የሁሉ ነገር ንድፍ፣ ይኼ ሁሉ የምታየው ሕንጣና ፎቅ ሳይቀር የንድፉ መነሻው 'ርሳስ ነው፡፡ አንዳንድ ማስታወሻም ካለ፣ ከጡህፍህ ሥር በስሱ ለማስታወስ ብትጥፍበት ትችላለህ፡፡ በቃልህ ከተያዘልህ በኋላ ታጠፈዋለህ አጎቴ ከሚገባው በላይ ሲያካብደው፣ የማውቀው እርሳስ የሆነ ሌላ ተአምር ነገር መሰለኝ!!

#ከዕለታት_ግማሽ_ቀን
አሌክስ-አብርሃም
ከገፅ 163-164 የተቀነጨበ.